Latest News

Image

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተገለፀ ።

‎ደባርቅ:- ህዳር 25/2018(የሰሜን ጎንደር ኮሙዩኒኬሽን )

‎በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ "ሰላም ለሃገራዊ አንድነትና መልካም ወንድማማችነት በሃይማኖት አስተምህሮ " በሚል መሪ ቃል ከሃይማኖት አባቶችና ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር ዞናዊ ጉባኤ ተካሂዷል ።

‎በጉባኤው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የደባርቅ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ጌትነት  ፀጋየ የመድረኩ አላማ በዞኑ የሚታየውን የእርስበርስ ግጭት በማምከን ሰላምን ማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል ። በአካባቢው የሚታየውን ጥፋትና ወድመት ለመታደግ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል ።

‎በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲ/ን ሸጋው ውቤ ላለፉት ሁለት አመታት ዞኑ ለከፋ ውድመት መዳረጉን ገልፀው ከልብ የመነጨ ሰላምን የሚሰብክ ሃዋሪያ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ። በዞኑ ያለው የሰላም እጦት ችግር የግብረገብነትና ፈጣሪን የሚፈራ ትውልድ አለማፍራት ስለሆነ የሃይማኖት አባቶች በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል ።

‎በጉባኤው የመወያያ ጽሁፍ  ያቀረቡት ኡስታዝ አብደላ ፈንቴ በእርስበርስ ግጭቱ ምክንያት በሃይማኖትና በህገ-መንግስቱ የተሰጡ የመኖርና የመማር መብት፣ ክቡር የሆነው የሰው ነፍስ የረከሰበትና የዞኑ ቱሪዝም እየተዳከመ መሄዱን አብራርተዋል ።

‎ተሳታፊዎችም በግራ ቀኝ እየሞቱ ያሉት ወንድሞቻችን ስለሆኑና መላ ህብረተሰቡን ከሰቃይ ለመገላገል ግጭቱ ን በሰላምና በድርድር ለመቋጨት ተግተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል ። እየተፈጸመ ያለው ድርጊት ከአከባቢው ባህልና ወግ ያፈነገጠ መሆኑ የገለፁት ተሳታፊዎች የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች የሚያቀርቡትን የመፍትሄ ሃሳብ መንግስትም በአዎንታ እንዲቀበለው አሳስበዋል ።

‎በጉኤው የሰሜን ጎንደር ዞን ሃገረስብከት ዋና ስራአስያጅ መላከ ሃይል አስምሮ ዋካ፣ የዞኑ እስልምና ምክርቤት ፕሬዝዳንት ኡስታዝ አህመድ የሱፍ፣የሃይማኖት አባቶች፣የሃገር ሽማግሌዎች ፣የደባርቅ  ወረዳና ከተማ የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል ።

2025-12-05 (8)

North Gondar Zone Map