
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተገለፀ ።
ደባርቅ:- ህዳር 25/2018(የሰሜን ጎንደር ኮሙዩኒኬሽን )
በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ "ሰላም ለሃገራዊ አንድነትና መልካም ወንድማማችነት በሃይማኖት አስተምህሮ " በሚል መሪ ቃል ከሃይማኖት አባቶችና ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር ዞናዊ ጉባኤ ተካሂዷል ።
በጉባኤው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የደባርቅ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ጌትነት ፀጋየ የመድረኩ አላማ በዞኑ የሚታየውን የእርስበርስ ግጭት በማምከን ሰላምን ማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል ። በአካባቢው የሚታየውን ጥፋትና ወድመት ለመታደግ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል ።
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲ/ን ሸጋው ውቤ ላለፉት ሁለት አመታት ዞኑ ለከፋ ውድመት መዳረጉን ገልፀው ከልብ የመነጨ ሰላምን የሚሰብክ ሃዋሪያ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ። በዞኑ ያለው የሰላም እጦት ችግር የግብረገብነትና ፈጣሪን የሚፈራ ትውልድ አለማፍራት ስለሆነ የሃይማኖት አባቶች በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል ።
በጉባኤው የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት ኡስታዝ አብደላ ፈንቴ በእርስበርስ ግጭቱ ምክንያት በሃይማኖትና በህገ-መንግስቱ የተሰጡ የመኖርና የመማር መብት፣ ክቡር የሆነው የሰው ነፍስ የረከሰበትና የዞኑ ቱሪዝም እየተዳከመ መሄዱን አብራርተዋል ።
ተሳታፊዎችም በግራ ቀኝ እየሞቱ ያሉት ወንድሞቻችን ስለሆኑና መላ ህብረተሰቡን ከሰቃይ ለመገላገል ግጭቱ ን በሰላምና በድርድር ለመቋጨት ተግተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል ። እየተፈጸመ ያለው ድርጊት ከአከባቢው ባህልና ወግ ያፈነገጠ መሆኑ የገለፁት ተሳታፊዎች የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች የሚያቀርቡትን የመፍትሄ ሃሳብ መንግስትም በአዎንታ እንዲቀበለው አሳስበዋል ።
በጉኤው የሰሜን ጎንደር ዞን ሃገረስብከት ዋና ስራአስያጅ መላከ ሃይል አስምሮ ዋካ፣ የዞኑ እስልምና ምክርቤት ፕሬዝዳንት ኡስታዝ አህመድ የሱፍ፣የሃይማኖት አባቶች፣የሃገር ሽማግሌዎች ፣የደባርቅ ወረዳና ከተማ የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል ።


.jpg)









.jpg)

.jpg)
.jpg)
.jpg)




